ስለ ተቋሙ
አቡ ሳይፍ ግሩፕ (ኤኤስጂ) በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከሞሮ ናሽናል ሊበሬሽን ፍሮንት ተገንጥሎ ወጣ፤ ይህ ቡድን በፊሊፒንስ ከሚገኙ እጅግ ከባድ ጥፋት ከሚያስከትሉ ሽብርተኛ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ በአል-ቃዒዳ ተጽዕኖ ስር የነበረው ይህ ቡድን፣ በምዕራባዊ ሚንዳናዎ እና ሱሉ አርኪፑላጎ ነጻ ኢስላማዊ መንግሥት እንዲመሰረት እንደሚፈልግ ይገልጻል፡፡ በቅርብ ጊዜ ከክልላዊ የአይሲስ ተባባሪ ድርጅት አይሲስ-ፊሊፒንስ ጋር ግንኙነት መስርቷል፡፡ ይህ ቡድን የቦንብ ጥቃቶችን፣ ግድያዎችን እና ለገንዘብ የሚደረግ እገታ በመፈጸም በመላው ፊሊፒንስ የሽብር ተግባራት ፈጽሟል፡፡
በመስከረም 28 ቀን 1990 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤኤስጂን በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በማለት በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት ሰይሞታል፡፡ በኋላ በመስከረም 23 ቀን 2001 ዓ.ም. ኤኤስጂ በሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ (ኤግዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 አባሪ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የኤኤስጂ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከኤኤስጂ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው ኤኤስጂ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡
