ስለ ተቋሙ
አል-ቃዒዳ በኢራቅ (ኤኪውአይ) በ1996 ዓ.ም. በሟች አሸባሪ አቡ ሙስዓብ አል-ዛርቃዊ ተመሠረተ፤ ይህ ቡድን አል-ቃዒዳ (ኤኪው) መሪ ኡሳማ ቢን ላዲን ታማኝ መሆኑን በይፋ ገልጾአል፡፡ በ1980ዎቹ፣ አል-ዛርቃዊ አል-ታውሂድ-ጂሃድ የተባለ ድርጅት አቋቋመ፤ በኋላ አል-ቃዒዳ በኢራቅ የዚህ ድርጅት ወራሽ ሆነ፤ ዓላማውም የዩናይትድ ስቴትስ እና የምዕራቡ ዓለም ወታደራዊ ኃይሎች በኢስላሙ ዓለም መገኘታቸውን እና የእስራኤልን ሕልውና እና ምዕራቡ ዓለም ለእስራኤል የሚሰጠውን ድጋፍ መቃወም ነው፡፡ አል-ዛርቃዊ በዩናይትድ ስቴትስ አመራር የ40 በላይ አገራት ጥምረት ኢራቅን በወረረበት የኢራቅ ነጻነት ኦፕሬሽን ወቅት ወደ ኢራቅ ተጓዘ፤ በሰኔ 1998 ዓ.ም. እስኪሞት ድረስ በኢራቅ ነበር፡፡ ኤኪውአይ ጥምር ጦሩን እና የኢራቅን የጦር ኃይል ኢላማ በማድረግ ተንቀሳቅሷል፤ ሲቪሊያኖችም ኢራቅን ለቅቀው እንዲወጡ ጫና ለማድረግ፣ ለዩናይትድ ስቴትስ የሚሰጥን ሕዝባዊ ድጋፍ ለመቀነስ እንዲሁም ተመልማዮችን ለመሳብ የጥቃቱ ዒላማ ነበሩ፡፡ በጥቅምት 1999 ዓ.ም. ኤኪውአይ ስሙን በይፋ ኢስላማዊ መንግሥት በኢራቅ ብሎ ቀየረ፡፡ በ2005 ዓ.ም. ከአል-ቃዒዳ ጋር የነበረውን ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ ኢስላማዊ መንግሥት በኢራቅ እና ሶሪያ (አይሲስ) ሆነ፡፡
በታኅሳስ 08 ቀን 1997 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤኪውአይን (እንዲሁም አይሲስ በመባል የሚታወቅ) በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በማለት በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት ሰይሞታል፡፡ ቀደም ብሎ በታኅሳስ 06 ቀን 1997 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤኪውአይን ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የኤኪውአይ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከኤኪውአይ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበው አይሲስ ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡
