ስለ ተቋሙ
ወሮታ ለፍትሕ ስለ አህመድ ኢማን አሊ ተብሎ ስለሚታወቀው ግለሰብ መረጃ ለሚሰጥ እስከ $3 ሚሊዮን ወሮታ ይከፍላል፡፡ አሊ በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጀት (ኤፍቲኦ) ተብሎ የተሰየመው የአል-ሸባብ ከፍተኛ አዛዥ ሲሆን ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በኬንያ የዚህ ቡድን መሪ ሆኖ አገልግሏል፡፡ እርሱም የቡድኑን ፀረ ኬንያ ኦፕሬሽኖች ይመራል፤ ቡድኑ በሶማሊያ የተሰማሩ የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ (አሚሶን) ኬንያዊ አባላት ኢላማ አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህ ጥቃት በጥር 2008 ዓ.ም. በኤል አዴ፣ ሶማሊያ በአንድ ወታደራዊ ሰፈር በወሰደው እርምጃ 140 ኬንያዊ የአሚሶን ወታደሮች ተገድለዋል፡፡
አሊ አል-ሸባብ በኬንያ መንግስት እና ሲቪሎች ላይ ለሚነዛው ፕሮፖጋንዳ በሃላፊነት ይፈለጋል፤ እንዲህ ካሉት ፕሮፖጋንዳዎች አንዱ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. በተቀረፀ ቪዲዮ በኬንያ የፀጥታ ሀይል ውስጥ የሚያገለግሉ የእስልምና ሃላፊዎችን አስፈራርቷል፡፡ እንዲሁም አሊ በናይሮቢ በሚገኙ ድሆች ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለአል-ሸባብ አባላት ይመለምላል፤ የአል-ሸባብን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ በመስጊዶች ገንዘብ አሰባስቧል፡፡
በየካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ ልዩ አለምአቀፍ ሽብርተኛ በማለት በስራ አስፈፃሚ ትእዛዝ (ኤክዘኪውቲቭ ኦርደር) 13224 እንደተሻሻለው መዝግቦታል፡፡ በዚህም መሰረት ሌሎች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የአሊ ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከአሊ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡ በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት በሚል ለተመዘገበ ድርጅት ሆን ብሎ የማቴሪያል ወይም የሀብቶች አቅርቦት ማድረግ፣ ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡ በተጨማሪም ለኤፍቲኦ አል-ሸባብ ሆን ብሎ የማቴሪያል ድጋፍ ወይም ሀብቶች ማቅረብ ወይም ለማቅረብ መሞከር ወይም ለማቅረብ መመሳጠር የወንጀል ድርጊት ነው፡፡
