ስለ ተቋሙ
የጃፓን ቀይ ጦር (ጄአርኤ) የተመሠረተው የጃፓን ኮሙኒስት ሊግ ቀይ ጦር አንጃ ከተለየ በኋላ በ1962 ዓ.ም. ነበር፡፡ የጃፓን ቀይ ጦር ያስቀመጠው ግብ የጃፓንን መንግሥት እና ንጉሣዊ ሥርዓት መገርሰስ ነው፡፡ የጃፓን ቀይ ጦር (ጄአርኤ) በዓለም ዙሪያ በርካታ ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን፣ ከእነርሱም መካከል በ1964 ዓ.ም. በእስራኤል በሎድ አየር ማረፊያ ላይ የተፈጸመው፣ የ26 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት፣ በ1967 ዓ.ም. በኳላ ላምፑር የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራ እንዲሁም በ1980 ዓ.ም. በኔፕልስ፣ ጣሊያን በዩኤስኦ ክለብ ላይ የተፈጸመው፣ የ5 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት ይገኙባቸዋል፡፡ የዚህ ቡድን መሪ በ1992 ዓ.ም. ታሰረ፤ ቡድኑም የመፍረስ ዕቅዱን በ1993 ዓ.ም. አሳወቀ፡፡
በመስከረም 28 ቀን 1990 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጃፓን ቀይ ጦር (ጄአርኤ)ን በተሻሻለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት ሕግ፣ በክፍል 219 መሠረት በውጭ አገር የሚገኝ ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ ሰይሞታል፡፡ በዚህም መሰረት በዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ የጃፓን ቀይ ጦር (ጄአርኤ) ንብረቶች እና ጥቅሞች ሁሉ ታግደዋል፣ ማናቸውም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከጄአርኤ ጋር በምንም አይነት ልውውጥ ላይ መሳተፍ አይፈቀድላቸውም፡፡
